ዛሬ የ ምናከብረው የአባቶች ቀን እንዴት ጀመረ?
By Ashenafi
Jun 21, 20261 min read
የአባቶች ቀን (Father's Day) ታሪክ ስንሰማ ብዙውን ጊዜ ዝም ብሎ በደስታና በጭብጨባ የተጀመረ ይመስለናል፤ ነገር ግን እውነታው ከአሰቃቂ አደጋ፣ ከታላቅ የልጅ ፍቅር እና ከብዙ ዓመታት ትግል ጋር የተያያዘ አስገራሚ ታሪክ አለው። እ.ኤ.አ. በታህሳስ 1907 በዌስት ቨርጂኒያ (አሜሪካ) በሚገኝ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ላይ አስከፊ ፍንዳታ ደረሰ። በዚህ አደጋ 361 ወንዶች (አብዛኞቹ አባቶች) በአንድ ጊዜ ህይወታቸውን አጡ። በዚህ ያዘነችው ግሬስ ጎልደን ክሌይተን የተባለች ሴት፣ በሟች አባቷና በእነዚህ አባቶች መታሰቢያነት አንድ የጸሎት ቀን እንዲደረግ ጠየቀች። ይህ የመጀመሪያው የአባቶች ቀን መታሰቢያ ነበር፤ ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚከበር በዓል ለመሆን አልበቃም ነበር። ዛሬ ለምናከብረው የአባቶች ቀን ትልቁን ድርሻ የምትወስደው ሶኖራ ስማርት ዶድ የተባለች ወጣት ናት። ሶኖራ ታሪኳ በጣም ልብ የሚነካ ነው፡-
የእናቶች ቀን በዓል ሲከበር በሰማች ጊዜ፣ ወዲያው ወደ አእምሮዋ የመጣው አባቷ ነበር። እናቷ ስድስተኛ ልጇን ስትወልድ በመሞቷ፣ አባቷ ዊልያም ስማርት የተባለው የርስ በርስ ጦርነት አርበኛ፣ ስድስቱንም ልጆች ብቻውን በብዙ መከራና ፍቅር አሳድጓቸዋል። እናቶች የሚከበሩትን ያህል፣ እንደ አባቴ ያሉ መስዋዕትነት የከፈሉ አባቶች ለምን አይከበሩም?" በማለት በ1910 ዘመቻ ጀመረች። የእሷ ጥረት ፍሬ አፍርቶ በሰኔ ወር 1910 ለመጀመሪያ ጊዜ በስፖኬን ዋሽንግተን የአባቶች ቀን ተከበረ። በ1972 (የእናቶች ቀን በዓል ከሆነ ከ62 ዓመታት በኋላ) ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን የአባቶች ቀን በየዓመቱ በሰኔ ወር ሶስተኛው እሁድ በይፋ እንዲከበር የአዋጅ ፊርማቸውን አኖሩ። ዛሬ የምናከብረው የአባቶች ቀን፣ በአንድ አባት ታላቅ የልጅ አስተዳደግ ፍቅር እና በአንዲት ልጅ ጽናት የመጣ ድንቅ ታሪክ ውጤት ነው:: History.com ስለ አባቶች ቀን አመጣጥ፣ በዓሉ በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ለምን ያህል ዓመታት ውድቅ ይደረግ እንደነበረ እና በ1972 በፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን አማካኝነት እንዴት ሙሉ በሙሉ ጸድቆ ብሔራዊ በዓል እንደሆነ ዝርዝር ታሪኩን ያስነብባል።
Filed under