የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል እና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ በማላዊ አድኖ ያዘ ::
By Ashenafi
Jul 30, 20261 min read
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል እና ከማላዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር፣ በብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽም የነበረውን አድነው ባሻው ውዳሞ የተባለ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ በማላዊ አድኖ በቁጥጥር ሥር በማዋል ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ እንዳመጣው አሳወቀ። ተጠርጣሪው ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል (በተለይም ከሀድያ እና ከንባታ ዞኖች) ወጣቶችን "ሕይወታችሁን ታሻሽላላችሁ" በሚል አታልሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያዘዋውር የነበረ ሲሆን፣ ከእያንዳንዱ ተጓዥ ከ600 ሺህ እስከ 800 ሺህ ብር ይጠይቅ ነበር።
ተጓዦችን በዕቃ መጫኛ ኮንቴነሮች፣ በተሳቢ እና በሸራ በተሸፈኑ መኪኖች አጭቆ ወደ ታንዛኒያ ካሻገረ በኋላ ጫካ ውስጥ ጥሏቸው ይፈረጥጥ ነበር።
አብዛኞቹ ወጣቶች ደቡብ አፍሪካ ሳይደርሱ በየሀገራቱ ፖሊስ ተይዘው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት የተቀጡ ሲሆን፣ እስራታቸውን ሲጨርሱም እስከ 170 ሺህ ብር ከፍለው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተገደዋል። ፌደራል ፖሊስ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲያደርግ በነበረው ክትትል ተጠርጣሪውን ለሕግ ማቅረቡን ገልጾ፣ በውጭ ሀገራት ያሉ ተመሳሳይ ወንጀለኞችን የማደኑ ሥራ እንደሚቀጥል አሳውቋል::
